አንጋፋው ተመራማሪ ጋቢሳ ኢጀታ ማን ናቸው?

አንጋፋው ተመራማሪ ጋቢሳ ኢጀታ ማን ናቸው?

GeneralStories

በሰሩት ስራ በአለም መድረክ እውቅናን ካተረፉ፣ በሳይንሱ አለም ባላቸው አበርክቶ ከተመሰገኑ እና ለወጣቱ ትውልድ ተምሳሌት መሆን ከቻሉ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች መሃከል ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኢጀታ ቀዳሚው ናቸው።

ጋቢሳ በሳይንሱ አለም ባላቸው አበርክቶ ብቻ ሳይሆን ባለፉበት የህይወት እጣ ውረድ ውስጥም የነበራቸው ባህርይ ለብዙዎቻችን ትምህርት የሚሆን ነው።

ጋቢሳ ህይወትን በባለጠጎች ወይም በተማሩ ሰዎች የቤት አልጀመሯትም። የስምንት አመት ልጅ እያለ እናት እና አባቱ በመለያየታቸው ጋቢሳን ያሳደገችው እናቱ ናት። እናቱ የተማረች አልነበረችም። እናቱ ጋቢሳን ለማሳደግ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፣ የመጀመሪያም የመጨረሻም ልጇ ነው፣ የምትተዳደረውም ጠላን በመሸጥ በምታገኘው ገቢ ነበር። የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያንም ህይወት ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት አለው። የጋቢሳ ህይወት ምንም እንኳን አስቸጋሪ በሆነ ህይወት ውስጥ እንኳን ብንገኝ የተሻለ ነገን መፍጠር እንደምንችል ማሳያ ነው።

ጋቢሳ አሁን ለደረሱበት የህይወት ስኬት ያበቃቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ለትምህርት የነበራቸው የጋለ ፍቅር ነው።

ጋቢሳ በ1942 አ.ም በወሎንኮሚ የተወለደ ሲሆን በልጅነቱ በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሯል። በትምህርቱም ጥሩ ስለነበር የታሰበው ዲያቆን እንዲሆን ነበር። በወቅቱ በከተማቸው የዘመናዊው ትምህርት አልነበረም። ሆኖም ግን በከተማቸው የነበሩ አንድ ባለሀብት ለራሳቸው እና ለጓደኞቻቸው ልጆች ትምህርት ቤት ይከፍታሉ። ጋቢሳ ወደዚህ ትምህርት ቤት ለመግባት አብዝቶ ቢፈልግም አልቻለም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት ቤቱ በወር 2 ብር ያስከፍል ስለነበር ነው። እናም ጠላ በመሸጥ የምትተዳደረው እናቱ ይህንን መክፈል አልቻለችም። ነገር ግን የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር በማናገር በቅናሽ አንድ ብር እየከፈለ እንዲማር ተደረገ።

ሆኖም ትምህርት ቤቱ እስከ ሶስተኛ ክፍል ብቻ ነበር የሚያስተምረው። ስለዚህ ጋቢሳ ከዚያ በኋላ ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አለም ዘመድ ጋር እየተመላለሰ እንዲማር ተደረገ። ይህንንም ሲማር 20 ኪ.ሜ በእግሩ ይጓዝ እንደነበር ተናግሯል። በእንደዚህ ሁኔታ እየተማረ የስምንተኛ ክፍል ፈተናውን ይወስዳል። የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መከታተል ነበረበት። ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረው በአምቦ ነበር። በአምቦ ዘመድ አልነበረም፣ እናም እናቱን' ምን ይሻላል? 'ብሎ ጠየቃት።  የእናቱ መልስ እጅግ የሚገርም ነበር " አንተ አምቦ ሔደህ መማር ካለብህ እዚህም ጠላ ሸጬ ነው የምኖረው፣ አምቦም ቢሆን ጠላ የሚጠጣ ሰው አለና እዛው ጠላ እየሸጥኩ አንተን አስተምርሀለው" ብላ እንደመለሰችለት ጋቢሳ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰበት ወቅት ተናግሯል።

ሆኖም ግን በፈተናው ጥሩ ውጤት ስለነበረው በጅማ አዳሪ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል እድል አገኘ። ይህ ለጋቢሳ ትልቅ እድል ነበር። ትምህርት ቤቱ ምግብ እና ልብስ ለተማሪዎቹ  ያቀርብ ስለ ነበር የጋቢሳን ልብ አሳርፎታል። በዚህም ሙሉ ትኩረቱ ትምህርት ላይ እንዲሆን ረድቶታል።

ከዚያም የመጀመሪያ ድግሪውን በእፅዋት ሳይንስ በአሁኑ ሀሮማያ ዪኒቨርሲቲ ተከታትሏል። ከዚያም የማስተርስ እና የፒኤችዲ ዲግሪውን  አሜሪካ ከሚገኘው ፔርዱ ዪኒቨርሲቲ አግኝቷል ።

የድህረ፟ ምረቃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ብኋላ ለአምስት አመት ወደ ሱዳን በመመለስ በማሽላ ላይ ጥናት ሲያካሒዱ ቆይተዋል። በዚህም ድርቅንና አቀንጭራ የተባለውን አረም የመቋቋም ችሎታ ያለውን የማሽላ ዝርያ ለአለም ህዝብ ማበርከት ችለዋል።

በዚህም ስራቸው በ2009 እ.ኤ.አ በአለም የምግብ ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል። ጋቢሳ ከሁለት መቶ በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን መድረግ ችለዋል ፣ በዚህም ከሀያ በላይ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

ጋቢሳ ምንም እንኳን ስማቸው በአለም አደባባይ ቢገንም የትውልድ ስፍራውን አልረሱም። ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአለም የምግብ ሽልማት ያገኙትን 250 ሺህ ዶላር ለልማት እንዲሆን አበርክተዋል።

ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት ወቅት በዚህ የህይወት ጉዟቸው፣ በደረሱበትት ስኬት እና በሰሯቸው መልካም ስራዎች የተገረመ አንድ ጋዜጠኛ ጋቢሳ የህይወት መርሔ ነው የሚሉትን አንድ አረፍተ ነገር እንዲፅፉ ወረቀት እና ብዕር ይሰጣቸዋል። እሳቸውም እንዲህ ብለው ፃፉ፣ " ትጋት እና ብርታት ከጭንቅላት ይበልጣል!"።  አዎ ትጋት እና ብርታት ከሁሉ ይበልጣል።